እንደ የፋይናንስ ተቋም፣ ደንበኞቻችን ምን ጊዜም ስለ ገንዘባቸው በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ ለመርዳት ዝግጁ ነን። የዋጋ ግሽበት ለብዙዎች ግራ የሚያጋባ ፅንሰ-ሀሳብ በመሆኑ፣ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ሁሉም ሰው ሊረዳው ይገባል።
- የዋጋ ግሽበት ምንድን ነው?
የዋጋ ግሽበት የሚከሰተው የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች አጠቃላይ ዋጋ ባልተለመደ ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሲጨምር ነው። ይህ ሊሆን የሚችለው በገበያ ውስጥ የሚንቀሳቀስ የገንዘብ መጠን እና የምርት ዋጋ፣ እንዲሁም ለተለያዩ እቃዎች እና አገልግሎቶች ፍላጎት መጨመርና በመሳሰሉት ምክንያቶች ነው።
- በቁጠባ ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
የዋጋ ግሽበት ጊዜና ሁኔታ ላይ በመመስረት የገንዘብን የመግዛት አቅም ይቀንሳል። ይህ ማለት በእጃችን ያለው የገንዘብ መጠን ወደፊት ዛሬ መግዛት ከሚችለው ያነሰ ይገዛል ማለት ነው። በመሆኑም፣ የዋጋ ግሽበት በቁጠባ እና በኢንቨስትመንት ላይ ያለውን ተጽእኖ አስቀድሞ መረዳት አስፈላጊ ነው።
- በዋጋ ግሽበት እንዳይጠቁ ምን ማድረግ ይኖርብዎታል?
ደንበኞቻችን እንዲቆጥቡ ስናበረታታቸው፣ የዋጋ ግሽበት በቁጠባ ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ እንዲገነዘቡም እንፈልጋለን።
በዋጋ ግሽበት እንዳይጠቁ ሊረዱዎት የሚችሉ አንዳንድ ጠቃሚ ነጥቦች እነሆ፡
- ወጪዎን መቆጣጠር፡ በዋጋ ግሽበት ወቅት የሸቀጦች እና የአገልግሎቶች ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ሊጨምር ስለሚችል፣ ወጪዎን ማስተካከል አስፈላጊ ነው። የማያስፈልጉትን ነገሮች መቀነስ እና በሚያስፈልጉት ላይ ብቻ ማተኮር ያስፈልግዎታል።
- የቁጠባ ልምድ ማዳበር፡ ካላቸው ነገር ላይ የሚቆጥቡ ሰዎች ከማይቆጥቡት ጋር ሲነፃፀር፣ የፋይናንስ ግባቸውን የማሳካት እድል አላቸው። “ትንሽ ነው” ብለው ሳይንቁት በተቻለ መጠን ከቆጠቡ፣ የአደጋ ጊዜ ወጪዎችዎን በቀላሉ ማከናወን ይችላሉ።
- የት እንደሚገዙ መለየት፡ ዕቃዎችን እና አገልግሎቶችን ሲገዙ ቅናሽ ቦታዎችን መፈለግ አለብዎት። በብዛት መግዛትም ዋጋን በመቀነስ ረገድ የራሱን ሚና ስለሚጫወት ከሻጩ ጋር ስምምነት ማድረግ አስፈላጊ ነው።
- የገቢ ምንጮችን ማሳደግ፡ ገቢዎ ከዋጋ ግሽበት ጋር የማይሄድ ከሆነ የኑሮ ሁኔታ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። በትርፍ ጊዜ መሥራትን የመሳሰሉ ገቢዎን የሚጨምሩ መንገዶችን ማሰብ አለብዎት።
- ገንዘብዎን በቋሚ ንብረቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ፡ እንደ መሬት እና ህንፃዎች ያሉ ቋሚ ንብረቶች በዋጋ ግሽበት ወቅት ጥሩ ዋጋ ሊኖራቸው ይችላል። በመሆኑም፣ ገንዘብዎን በእንደዚህ ዓይነት ንብረቶች ላይ ካዋሉ፣ ለወደፊቱ የገንዘብዎ ዋጋ እንዳይቀንስ ይረዳዎታል። ይሁን እንጂ፣ ማንኛውም የኢንቨስትመንት ሥራ ያልታሰበ ኪሳራ ሊኖረው እንደሚችል በመረዳት ከመጀመርዎ በፊት የባለሙያ ምክር ማግኘት አስፈላጊ ነው።
በመጨረሻም፣ በዋጋ ግሽበት ወቅት ወጪዎ ላይ መጠንቀቅ፣ ያለዎትን መቆጠብ እና ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለግ እንደሚኖርብዎ መረዳት ያስፈልጋል።