- የማሻሻያው ምክንያት
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም ባደረገው የህግ እና ቁጥጥር ሪፎርም ባንኮች የተለያዩ የአሰራር እና አስተዳደር ለውጦችን እንዲያደርጉ የሚያስገድዱ ድንጋጌዎችን የያዙ መመሪያዎችን አውጥቷል፡፡ በተለይም የባንክ ቦርድ አወቃቀር፣ ኃላፊነቶችና ተግባራት እንዲሁም በአጠቃላይ በባንክ አስተዳደርና አመራር ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ተግባር እና ኃላፊነትን በተመለከተ ሰፊ ለውጦች ተደርጓል፡፡ በመሆኑም የባንኩን መመስረቻ ጽሑፍ መመሪያዎቹ ይዘው ከመጡት ለውጦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የሚከተሉት የማሻሻያ ሀሳቦች ቀርበዋል፡፡
- ማሻሻያ የተደረገባቸው አንቀጾች ዝርዝር
1.አንቀጽ 21፡ የጥቅም ግጭት
- የተደረገው ማሻሻያ- የሚከተለው አዲስ ንዑስ አንቀጽ (7) ተጨምሯል፡፡
‘’7. ባንኩ ተፈጻሚነት ባለው ህግ አግባብ የጥቅም ግጭትን የሚመዘገብበት መዝገብ ይይዛል፡፡’’
- አንቀጽ 23፡ የባንኩ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ስልጣንና ተግባራት
- የተደረገው ማሻሻያ- በመመስረቻ ጽሑፉ አንቀጽ 23 (3) (መ) እና (ሠ) ላይ የሚከተለው ማሻሻያ ተደርጓል፡-
‘’መ. በዳይሬክተሮች ቦርድ ተዘጋጅቶ የቀረበለትን የቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ አፈፃፀም ፖሊሲና የአሰራር ስነ-ስርዓት ያጸድቃል፣ ያሻሽላል፡፡
ሠ. የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫ በሚካሄድበት ጉባዔ ዕለት የምርጫ ሂደቱን የሚያስፈጽም ጊዜያዊ የቦርድ የጥቆማና አስመራጭ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ኮሚቴው እንዲቋቋም ያደርጋል።’’
- አንቀጽ 26- የዳይሬክተሮች ቦርድ
- የተደረገው ማሻሻያ- ነባሮቹ ንዑስ አንቀጽ 26(1) እና 26(6) ላይ የሚከተለው ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
- ‘’ባንኩ በመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው በሚመረጡ፣ በአንድነት ሥራቸውን በሚያካሄዱና ለባንኩ እንደራሴ በሚሆኑ 12 (አስራ ሁለት) አባላት ባሉት አንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ ይመራል፡፡’’
- ቦርዱ ከአባላቱ መካከል ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ ይመርጣል፤ እንደዚሁም ተፈጻሚነት ባለው ህግ አግባብ ለስራው አስፈላጊ የሆኑ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል፡፡”
4.አንቀጽ 28፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ አወቃቀር
- የተደረገው ማሻሻያ- በነባሮቹ ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ ማሻሻያ የተደረገባቸው ሲሆን፣ ንዑስ አንቀጽ 3 ከመመስረቻ ጽሑፉ እንዲወጣ ተደርጎ 3 አዳዲስ ንዑስ አንቀጾች እንደሚከተለው ተጨምረዋል፡፡
- ‘’የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎችን (ሲኒየር ኤክሰኪቲቭ አፊሰሮች) ጨምሮ ከባንኩ ሠራተኞች እና ገለልተኛ ከሆኑ ዕጩዎች ውስጥ የተመረጡ ዳይሬክተሮችን ያካትታል፡፡
- የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ዕድገት ደረጃ፣ የስራውን ውስብስብነት እና የአደጋ ተጋላጭነት መገለጫን በሚመጥን፣ ስራው የሚፈልገውን የእውቀትና ሙያ ስብጥርን ባገናዘበ፣ እንዲሁም ልዩነትን አካታች በሆነ መልኩ መዋቀር አለበት፡፡ የሞያ/እወቀት ስብጥሩ የባንክ፣ የፋይናንስ፣ የሂሳብ አያያዝ፣ የማኔጅመንት፣ የኢኮኖሚክስ፣ የህግ፣ የንግድ አስተዳደር፣ የኦዲት፣ የመረጃ ቴክኖሎጂ፣ የኢንቨስትመንት አመራር፣ እና የዘላቂነት (ሰስቴናቢሊቲ) ሙያዎችን ያካትታል፡፡
- የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ፡
ሀ. ተጽዕኖ ፈጣሪ ባልሆኑ ባለአክሲዮኖች ብቻ የሚጠቆሙ እና የሚመረጡ 4 (አራት) ዳይሬክተሮች፤
ለ. በሁሉም የባንኩ ባለአክሲዮኖች የሚጠቆሙ እና የሚመረጡ 4 (አራት) ዳይሬክተሮች፤ እና
ሐ. ስራ ላይ ባለው የዳይሬክተሮች ቦርድ ተመልምለው በሚቀርቡ እና በሁሉም የባንኩ ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ 4 (አራት) ገለልተኛ የሆኑ ዳይሬክተሮችን በማካተት ይዋቀራል፡፡
- የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አወቃቀር የፆታ ውክልናን ያረጋገጠ መሆን አለበት፤ በዚሁ መሰረት ከአጠቃላይ የባንኩ ቦርድ አባላት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ (2) ሴቶች መሆን አለባቸው፡፡
- የባንኩን ዋና ስራ አስፈጻሚን እና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎችን (ሲኒየር አክሰኪቲቭ አፊሰሮችን) ጨምሮ እጅግ ቢበዛ ሁለት (2) የባንኩ ሠራተኞች በቦርድ አባልነት ሊመረጡ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን የባንኩ ጸሐፊ የቦርድ አባል ሆኖ መመረጥ አይችልም፡፡
5.አንቀጽ 29፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሥልጣንና ተግባራት
- የተደረገው ማሻሻያ- ንዑስ አንቀጽ 29 (11) በሁለት ንዑስ አንቀጾች ተከፍሎ (11 እና 12)፣ ንዑስ አንቀጽ (12)፣ (16)፣ (19) እና (22) ላይ ደግሞ ማሻሻያ ተደርጎዋል፤ እንዲሁም 4 አዳዲስ ንዑስ አንቀጾች ተጨምረዋል፡፡
- ‘’የቦርዱ የጥቆማ እና የስራ ዋጋ ኮሚቴ (Nomination and Remuneration Committee) በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ መሠረት የባንኩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ሹመት፣ ምደባና ስንብት ላይ ይወስናል፡፡
- የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ መሠረት የባንኩ ፀሐፊ ሹመት፣ ምደባና ስንብት ላይ ይወስናል፡፡
- ተፈጻሚነት ባለው ህግ መሰረት ሀላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስፈልጉትን የተለያዩ ቋሚና ጊዜያዊ ኮሚቴዎችን ያቋቁማል፣ በአግባቡ መስራታቸውንም ያረጋግጣል፡፡
- ግልጽ የሆነ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ አፈፃፀም ፖሊሲ እና የአሰራር ስነስርዓትን አዘጋጅቶ እንዲጸድቅ ለመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ያቀርባል፡፡
- በዚህ መመስረቻ ጽሑፍ አንቀጽ 23 (3)(ቀ) ስር የተቀመጠው የመደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ስልጣን እንደተጠበቀ ሆኖ ተፈጻሚነት ባለው ሕግና በብሔራዊ ባንክ መመሪያ መሰረት በባንኩ እና ከባንኩ ጋር ቅርበት ባላቸው ሰዎች ወይም ድርጅቶች መካከል የሚደረግ ስምምነትን ስምምነቱ ከመፈጸሙ በፊት በቅድሚያ ይፈቅዳል፣ ከፈቀደ በኋላም ወዲያውኑ ለኦዲተሮች ያሳውቃል፣
- ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል በሚያደርገው የአይነት ወይም የገንዘብ ስጦታ ላይ ይወስናል፤ እንዳስፈላጊነቱም ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚያስችሉ እና በዚሁ ዙሪያ የሚሰሩ ፋውንዴሽኖችን አንዲያቋቁም በሚቀርብ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ይወስናል፣
ተጨማሪ የዳይሬክተሮች ቦርድ ኃላፊነትና ተግባራት፡
- ‘’ባንኩ በልዩ ልዩ የፋይናንስና ተያያዥ ስራ ዘርፎች ላይ በማተኮር የሚሰሩ ተቀጥላ ኩባንያዎችን እንዲያቋቁም በሚቀርብ የውሳኔ ሀሳብ ላይ ይወስናል፤
- የባንኩን የስነ-መግባር መርሆች እና እሴቶችን (Corporate Culture and Value) ይቀርጻል፤ ለሚመለከታቸው የባንኩ አካላት በማሳወቅ ስራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፣
- ባንኩ ከዘላቂነት (Sustainability) ጋር ለተያያዙ የአደጋ ስጋቶች እና እድሎች (sustainability-related risks and opportunities) በሚሰጠው ምላሽ ላይ ቁጥጥር ያደርጋል፤ የባንኩ ከፍተኛ አመራር እነዚህን የአደጋ ስጋቶችን እና እድሎችን ከመቆጣጠር አንጻር ያለውን ሚና እና ኃላፊነቶችን በግልጽ ያስቀምጣል፣
- የባለድርሻ አካላት ከባንኩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እና ሂደቱን ይቆጣጠራል፤ እንዲሁም በባለድርሻ አካላቱ የሚነሱ ሀሳቦች እና ስጋቶች በባንኩ ስትራቴጂ ውስጥ መካተታቸውን ያረጋግጣል፣‘’
- አንቀጽ 30፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ
- የተደረገው ማሻሻያ- ነባሮቹ ንዑስ አንቀጽ 3 እና 4 በማሻሻያው አዲስ ንዑስ አንቀጽ 4 ስር እንዲካተቱ ተደርጎ ሁለት አዳዲስ ንዑስ አንቀጾች (ንዑስ አንቀጽ 2 እና 4) እንደሚከተለው ተጨምረዋል፡፡
2.‘’የባንኩ የቦርድ ሰብሳቢ መሆን የሚችለው ባለአክሲዮን የሆነ ዳይሬክተር ነው፤ ከሠራተኛ የተመረጠ እና ገለልተኛ የሆነ ዳይሬክተር የቦርድ ሰብሳቢ መሆን አይችልም፤
- በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ማኅበርን/ተቋምን ወክሎ የቦርድ አባል የሆነ ሰው የቦርድ ሰብሳቢ ሆኖ መመረጥ ይችላል፡፡ ሆኖም ተወካዩ ኃላፊነቱን ከተወ ወይም በኃላፊነቱ መቀጠል የማይችልበት ሁኔታ ከተፈጠረ በዚህ መመስረቻ ጽሑፍ አንቀጽ 28(6) መሰረት ወካዩ ይሄንኑ ለባንኩ በጽሑፍ ለማሳወቅ እና ሌላ ተወካይ ለመመደብ ያለበት ሃላፊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በማህበሩ/በተቋሙ በተተኪነት የሚመደበው ተወካይ የቦርድ ሰብሳቢነቱን ቦታ የመውረስ መብት አይኖረውም፡፡ በመሆኑም ከኃላፊነቱ የለቀቀውን ሰብሳቢ የሚተካ ሌላ አባል በቦርዱ የሚመረጥ ይሆናል፡፡
- ሰብሳቢው በሕግ እና በዚህ መመስረቻ ጽሑፍ የተሰጡትን ስልጣን እና ተግባራት ይኖሩታል፡፡ ይህ ጠቅለል ያለ አነጋገር እንደተጠበቀ ሆኖ ሰብሳቢው የሚከተሉ ኃላፊነቶች እና ተግባራት ይኖሩታል፡–
ሀ. የባንኩን ውጤታማነት በሚያረጋግጥ መልኩ ቦርዱን መምራት፣
ለ. በዳይሬክተሮች ቦርድና በጠቅላላ ጉባኤ የተላለፉ ውሳኔዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣
ሐ. ለዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባዎች አጀንዳ ማዘጋጀት ወይም እንዲዘጋጅ ማድረግ፤ የቦርድ ስብሰባዎችን መጥራት፣ በግልጽነት፣ የሀሳብ ነጻነትና ልዩነትን በሚያከብር እና ጥልቅ ውይይትንና ክርክርን በሚያበረታታ መልኩ ስብሰባውን መምራት፤
መ. በዳይሬክተሮች ቦርድ የተጠራውን ጠቅላላ ጉባዔ መምራት፡፡
- አንቀጽ 31፡ የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ እና ውሳኔ
- የተደረገው ማሻሻያ- በንዑስ አንቀጽ 1 እና 3 ላይ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፣ የነባሩ ንዑስ አንቀጽ 5 ድንጋጌ ከመመስረቻ ጽሑፉ ወጥቶ በምትኩ ሌላ ድንጋጌ ተካቶዋል።
- ‘’የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰባ የሚያካሄድበትን ሁኔታ የሚደነግግ ደንብ ማውጣት አለበት፡፡ በዚሁ ደንብ ውስጥ በሚወሰን ቀን እና ቦታ ቢያንስ በሩብ ዓመት አንድ ጊዜ ስብሰባውን ማካሄድ ይኖርበታል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ሰብሳቢው ሌሎች የዳይሬክተሮች ቦርድን ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡
3.ቦርዱ በቪድዮ ኮንፈረንስ ወይም ሌላ የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ዘዴ በመጠቀም አስቸኳይ ስብሰባዎችን ማካሄድ ይችላል፡፡ የኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ዘዴው የተሰብሳቢዎችን ማንነት ለመለየት የሚያስችል እንዲሁም ውጤታማ ተሳትፎን የሚያረጋግጥ፣ ቢያንስ የተሳታፊዎችን ድምጽ ሳይቆራረጥ የሚያስተላልፍ፣ ምስጢራዊነትን ለመጠበቅ የሚያስችል እና ተሰብሳቢዎቹ በአንድ ጊዜ መሳተፍ እንዲችሉ የሚፈቅድ መሆን አለበት፡፡
5.የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት በእያዳንዱ የስብሰባ አጀንዳ ላይ ለመወያየት የሚያስችላቸውን በቂ ቅድመ ዝግጅት አድርገው ስብሰባው ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡’’
- አንቀጽ 33፡ ለባንኩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ
- የተደረገው ማሻሻያ- ንዑስ አንቀጽ 33(2) እና (6) ላይ የሚከተለው ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
‘’2. በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ስር የተዘረዘሩት የተፈጥሮ ሰዎች የትዳር አጋር ወይም ከነዚህ ሰዎች ጋር ተፈፃሚነት ባለው ሕግ መሰረት የስጋና የጋብቻ ዝምድና ያላቸው ሰዎች ከባንኩ ጋር ቅርበት ካላቸው ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ይካተታሉ፡፡
6.ባንኩ ለባንኩ ቅርበት ካላቸው ሰዎች መዝገብ በተጨማሪም እያንዳንዱ ከባለአክሲዮኖች የተመረጠ የባንኩ የቦርድ አባል ያለውን የአክሲዮን ብዛትና ዋጋቸውን የሚያመለክት መዝገብ በዋናው መስሪያ ቤቱ ይይዛል፡፡’’
- አንቀጽ 35፡ የባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሥልጣንና ተግባር
- የተደረገው ማሻሻያ- አንቀጽ 35(6) በተለያዩ ሁለት ንዑስ አንቀጾች (35.6) እና (35.7) ተከፍሎ የሚከተለው ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡
‘’6. ዕጩ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎችን መልምሎ ሹመታቸውን በዋናው ቦርድ እንዲያጸድቅ ለቦርዱ የጥቆማ እና የስራ ዋጋ ኮሚቴ(Nomination and Remuneration Committee) ያቀርባል፣
7.የባንኩን ፀሐፊ በመመልመል ሹመቱ እንዲጸድቅ ለቦርድ ያቀርባል፡፡’’
- አንቀጽ 37፡ የባንኩ ፀሐፊ ሥልጣንና ተግባር
- የተደረገው ማሻሻያ- ነባሩ ንዑስ አንቀጽ 37(8) ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ሌላ ሶስት አዳዲስ ንዑስ አንቀጾች ተጨምረዋል፡፡
‘’8. የባንኩን የባለአክሲዮኖች መዝገብ፣ የዳይሬክተሮች መዝገብ፣ ከባንኩ ጋር ቅርበት ያላቸው ሰዎች መዝገብ እና የጥቅም ግጭት መዝገብን በትክክል ማደራጀት፣ በአግባቡ መያዝ እና መዝገቦቹ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን ያካተቱ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣
ተጨማሪ የጸሐፊው ስልጣን እና ተግባራት፡
- የባንኩን መልካም አስተዳደር እና የመልካም አስተዳደር መስፈርቶች መሟላታቸውን በቅርበት
መከታተል፣
- የቦርድ እና የኮሚቴ ስብሰባዎችን የጊዜ መረኃ ግብር ማዘጋጀት፣
- የቦርድ አባላት ውጤታማ የሆነ የአቅም ግንባታ እና ስልጠና መውሰዳቸውን ማረጋገጥ፣’’
- አንቀጽ 39 (9)፡ የባንኩ ኦዲተሮች ተግባር፣ ኃላፊነት እና ስልጣን
- የተደረገው ማሻሻያ- በንዑስ አንቀጽ 39(9) ላይ የሚከተለው ማሻሻያ ተደርጓል፡፡
‘’9. በባንኩ እና ከባንኩ ጋር ቅርበት ባላቸው ሰዎች መካከል የሚደረግን ስምምነት አስመልክቶ በዚህ መመስረቻ ጽሑፍ አንቀጽ 23 (3) (ቀ) እንዲሁም በንግድ ሕጉ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች መሰረት ውሳኔ ለመስጠት ይረዳ ዘንድ ስለውሉ ሁኔታ፣ የተፈፀመውን ክፍያ አይነትና መጠን፣ እንዲሁም ለጥቅም ግጭት ምክንያት የሆነውን የቅርበት ሁኔታ የሚገልፅ በቂ መረጃ በማካተት የጽሑፍ ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባኤ ማቅረብ፣’’
ከላይ በቀረበው መልኩ በያንዳንዱ አንቀጾች ላይ የተደረገው ማሻሻያ እንደተጠበቀ ሆኖ የተደረገው ማሻሻያ በንዑስ አንቀጾች ቅደም ተከተል ላይ ለውጥ ያስከተለባቸው አንቀጾችን በተመለከተ የሀሳብ ፍሰቱን በጠበቀ እና ተያያዥነታቸውን ባገናዘበ መልኩ ተገቢው የቅደም ተከተል ማስተካከያ ተደርጎባቸዋል፡፡ አንቀጽ 28፣ 29፣ 30 እና 37 በዚሁ መሰረት የንዑስ አንቀጾች ቅድመ ተከተል ማሻሻያ እና ሽግሽግ የተደረገባቸው አንቀጾች ናቸው፡፡