‘የለውጥ ቀንድ’ በመባልም ተሞካሽቷል
የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የ20ኛ ዓመት የምስረታ ከብረ በዓል፤ የባንኩ ደንበኞች፣ ባለድርሻ አካላት፣ የመንግስት የሥራ ኅላፊዎችና ሌሎች ተጋባዠ እንግዶች በተገኙበት በሸራተን አዲስ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል። በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የብሄራዊ ባንክ ገዢ ክቡር አቶ ማሞ ምህረቱ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በሀገራችን ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ፣ ብዙ ፈጠራዎችን ካስተዋወቁና ማህበረሰብ ተኮር ከሆኑ ባንኮች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በስትራቴጂክ አወቃቀሩና በትራንስፎርሜሽን እሳቤዎች የ21ኛው ክፍለ ዘመን የባንክ አሠራር አርዓያ ለመሆን መቻሉን በንግግራቸው ገልጸዋል።
በሞባይል ዋሌቱ በኮፔይ ኢ-ብር በደረሳቸው 17 ሚሊዮን ደንበኞቹ በተከናወኑ ግብይቶች ብር 3 ትሪሊዮን በሚደርስ ግብይቱ የሞባይል ገንዘብ ግብይት የአፈጻጸም ደረጃው ከሀገሪቱ መሪ የሞባይል ዋሌቶች አንዱ በመሆንና በሚሰጠው ከማስያዢያ ነጻ ‘ምቹ’ ዲጂታል ብድር ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ንግዶችን በማጎልበት፤ የፋይናንስ ተደራሽነትን ምንነት በመለወጥ የአካታች ፋይናንስ አንጸባራቂ ምሳሌ ለመሆን ችሏል ብለዋል። የብሄራዊ ባንኩ ገዢ አክለውም የባንኩ እሴቶች ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ራዕይ ጋር አብረው የሚሄዱ ስለመሆናቸው አድናቆትን በመቸር ባንኩን ‘የለውጥ ቀንድ’ በማለት አሞካሽተዋል።
የአሠራር አድማሱን በማስፋት አካታችነትን ተግባራዊ ያደረገው የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ‘ማህበረሰብን በማብቃት የኑሮ ደረጃውን የመቀየር ዓላማን አንግቦ፤ በላቀ የዲጂታል ፈጠራ የታገዘ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዕውን በማድረግ ላይ መሆኑን በንግግራቸው ያስታወቁት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደርቤ አስፋው፤ ቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት በማድረግ የማህበረሰብ ችግር ፈቺና አኗኗርን አቅላይ ዲጂታል አገልግሎቶችን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ባንኩ ራዕይና ተስፋን ለሰነቁ ሥራ ፈጣሪዎች በ’ምቹ’ ብድር ያለማስያዣ የሰጠው ብር 20 ቢሊየን፣ በፋርም ፓስ የተከናወኑት ከ440 ሚሊዮን ብር በላይ መጠን ያላቸው ግብይቶች፣ ለገንዘብ ቁጠባና ብድር የ/ኅ/ሥ ማህበራትና ዩኒየኖች ዲጂታል አሠራርን ያስተዋወቀው SACCO–Link ትግበራ፣ በዘመናዊው ATM በአጭር ጊዜ ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ገቢ መደረግ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከሉ በባንኩና ከሌሎች አጋሮች ጋር በጥምረት በርካታ አገልግሎቶች በመበልጸግ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን፣ የስማርት ቅርንጫፎች ሥራ ላይ መዋል፣ ከአካባቢ ተፈጥሮ ጋር የተዋደዱት በታዳሽ ኃይል የሚሠሩ ኢኮ ቅርንጫፎች መስፋፋት፣ ፈጣንና በአነስተኛ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ ፋስት ፔይና ለሀገራችን የመጀመሪያው የሆነው በብሎክ ቼን ቴክኖሎጂ የታገዘው ኮፕ ሬሚት ተግባራዊ መሆን፤ ባንኩ በዲጂታሉ መስክ ያሳየውን እመርታ የሚያረጋግጥ መሆኑ ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት በማደግ አጠቃላይ ሀብቱ ብር 189.4 ቢሊዮን የሆነ፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ባለፉት 9 ወራት ከተሰበሰበው ብር 52.3 ቢሊዮን ጋር ብር 169.45 ቢሊዮን የደረሰ፣ 14.5 ሚሊዮን ደንበኞች ያሉት፣ የ745 ቅርንጫፎች ባለቤት፣ የ15,000 ዜጎች አሰሪ የሆነ ግዙፍ ባንክ ለመሆን ችሏል።
ባንኩ ‘የፕሮጀክት 20 ለ 20ኛ ዓመት ክብረ በዓል’ በሚል መጠሪያ በተለያዩ ማህበራዊ ጠቀሜታ ባላቸው ክንዋኔዎች ለአንድ ወር ሲያከብር መቆየቱ ይታወቃል።