ለኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ አ.ማ ባለአክሲዮኖች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማ እና ምርጫ መስፈርት እና የጥቆማ ስነ-ስርዓትን ስለማሳወቅ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች አስተዳደር መመሪያ ቁጥር SBB/91/2024 አንቀጽ 9.3 መሰረት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ መስፈርት ምርጫ ከሚካሄድበት ጠቅላላ ጉባዔ አንድ ወር አስቀድሞ ለባለአክሲዮኖች መገለፅ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በመመሪያው አንቀጽ 9.4 መሰረት ደግሞ የጥቆማ ስነ-ስርዓቱም ከጉባዔው ቀን በፊት ለባለአክሲዮኖች መገለጽ አለበት፡፡ በመመሪያው እና በባንኩ ፖሊሲ እና ፕሮሲጀር መሰረት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ከባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ ሠራተኞች እና ነጻና ገለልተኛ ከሆኑ ዕጩዎች ውስጥ ከሚመረጡ ዳይሬክተሮች ይዋቀራል፡፡ በዚሁ አግባብ የባንኩ የቦርድ አባላት ጥቆማ እና ምርጫ መስፈርቶች እና የጥቆማ ስነ-ስርዓቱ እንደሚከተለው የቀረበ ሲሆን፣ ባለአክሲዮኖችም ታህሳስ 19 ቀን 2017 ዓ.ም በሚያካሄደው 20ኛ የባለአክሲኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በመገኘት አስፈላጊውን መስፈርቶች የሚያሟሉ እና ብቁ የሆኑ የቦርድ አባላትን እንዲጠቁሙና እንዲመርጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
- የባንኩዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ ለመመረጥ ዕጩዎች ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች
1.1 አጠቃላይ መስፈርት
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኖ ለመመረጥ የሚጠቆም ሰው ተፈጻሚነት ባላቸው ሕጎች፣ በብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች እና በባንኩ የውስጥ ደንቦች ላይ የተቀመጡ የብቃት እና አግባብነት መመዘኛ መስፈርቶችን (fitness and propriety criteria) ማሟላት አለበት፡፡
1.2 ዝርዝር መስፈርቶች
ማንኛውም በግልም ሆነ በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸውን ማህበራት ወይም ተቋማትን ወክሎ ለባንኩ የቦርድ አባልነት የሚጠቆም ባለአክሲዮን፣ እንዲሁም ሠራተኛ እና ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ ዕጩ (Independent Directors) የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል፡፡
ማንኛውም በግልም ሆነ በህግ የሰውነት መብት የተሰጣቸውን ማህበራት ወይም ተቋማትን ወክሎ ለባንኩ የቦርድ አባልነት የሚጠቆም ባለአክሲዮን፣ እንዲሁም ሠራተኛ እና ነጻ እና ገለልተኛ የሆነ ዕጩ (Independent Directors) የሚከተሉትን መስፈርቶች ማሟላት ይኖርበታል፡፡
- ታማኝ፣ ሀቀኛ፣ ታታሪ፣ መልካም ስምና ዝና ያለው፤ በማጭበርበር፣ እምነት በማጉደል፣ ትክክለኛ ያልሆነ የሂሳብ መግለጫ በማቅረብ እና ተፈፃሚነት ባለው ህግ መሠረት ለቦርድ አባልነት ብቁ በማያደርግ ተመሳሳይ ወንጀል ጥፋተኝነቱ ያልተረጋገጠ፣
- በኪሳራ ምክንያት ንብረቱ ለዕዳ ማቻቻያነት ያልዋለ፣ የባንክ ብድር ባለመክፈሉ ምክንያት ንብረቱ በሐራጅ ያልተሸጠ፤ የሚመራው ወይም ዳይረክተር የሆነበት ድርጅት ከገንዘብ ተቋማት የተበደረውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ብድሩ ወደ ጤናማ ያልሆነ የብድር ደረጃ ያልገባበት፣
- በቂ ስንቅ/ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ሰጥቶ ሂሳቡ ያልተዘጋበት፣ እንዲሁም ግብር ባለመክፈል ተከሶ ጥፋተኛ ያልተባለ፣
- ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት የሚያስፈልገውን በቂ ጊዜ ያለው፣
- የራሱን ሃሳብ በነፃነት የሚያራምድ እና የጥቅም ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ ነገሮችን የሚያስወግድ፣
- ከአራት በላይ በሆኑ ተቋማት ውስጥ በቦርድ ዳይሬክተርነት እየሰራ ያልሆነ፣ እና በሌላ የፋይናንስ ተቋም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወይም ሰራተኛ ያልሆነ፣
- ዕድሜው ከ30 ዓመት ያላነሰ ከ70 ዓመት ያልበለጠ፣
1.3.ከባንኩ ባለአክሲዮኖች ፤ ከባንኩ ዋና ስራ አስፈጻሚ እና ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚዎች እና ሠራተኞች ውስጥ ለሚጠቆሙ ዕጩዎች ተጨማሪ መስፈርቶች
ከላይ በተ.ቁ 1.1 እና 1.2 ስር ከተቀመጡት በተጨማሪ ባለአክሲዮን ወይም ሠራተኛ የሆነ ዕጩ፡-
- ከታወቀ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቢያንስ የመጀመሪያ ድግሪ ወይም ተመጣጣኝ የትምህርት ደረጃ ያለው እና ለሥራው ተፈላጊነት ባለው የሙያ ዘርፍ (በባንኪንግ ወይም በፋይናነስ፣ በአደጋ ስጋት(ሪስክ) አስተዳደር፣ በሂሳብ አያያዝ፣ በንግድ ሥራ አስተዳደር፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሕግ፣ በኦዲት ስራ፣ በመረጃ ቴክኖሎጂ፣ በኢንቨስትመንት አስተዳደር፣ በዘላቂነት /Sustainability/ እና በተዛማጅ የሙያ ዘርፍ ቢያንስ ከሰባት (7) ዓመታት ያላነሰ የሥራ ልምድ ያለው፣ እና
- ምርጫው ከሚካሄድበት ጉባዔ አስቀድሞ ባሉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት በባንኩ ባለአክሲዮንነት ተመዝግቦ የቆየ መሆን አለበት፡፡
1.4. ነጻና ገለልተኛ የሆኑ ዕጩ ዳይሬክተሮች
በብሔራዊ ባንክ የባንኮች አስተዳደር መመሪያ መሰረት ስራ ላይ ያለው ቦርድ በመመሪያው አንቀጽ 2.9፣ እንዲሁም በመመሪያ ቁጥር SBB/89/2024 አንቀጽ 2.8 እና 5.1.2 ስር በተቀመጡ መስፈርቶች መሰረት ነጻና ገለልተኛ የሆኑ የቦርድ ዕጩዎችን በመመልመል ዝርዝራቸውን ለጊዜያዊ የጥቆማ እና አስመራጭ ኮሚቴ የሚያስረክብ ሲሆን ኮሚቴው ደግሞ ዝርዝሩን ለጉባዔው አቅርቦ የዳይሬክተሮቹ ምርጫ ይከናወናል፡፡ በዜግነት ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ሰው የባንኩ ነጻና ገለልተኛ ዳይሬክተር ሆኖ መመረጥ ይችላል፡፡
- የቦርድአባላት ጥቆማ ስነ–ስርዓት
- ጊዜያዊኮሚቴ ማቋቋም
የቦርድ አባላት ምርጫ በሚካሄድበት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የመጀመሪያ አጀንዳ የሚሆነው የጥቆማ እና ምርጫ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት ሂደቱን የሚመራ እና የሚያስተባብር ጊዜያዊ የቦርድ አባላት የጥቆማ እና አስመራጭ ኮሚቴን ማቋቋም ነው፡፡ ኮሚቴው የሚቋቋመው በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ውስጥ በተቀመጠው አግባብ የኮሚቴ አባላቱን በጉባዔው በመምረጥ ይሆናል፡፡
- የጥቆማስነ–ስርዓት
ከቦርድ አባላት የጥቆማ ሂደት እና ስነ-ስርዓት ጋር ተያይዞ የሚከተሉት ዋና ዋና ነጥቦች ከግንዛቤ ሊወሰዱ ይገባል፡፡
- የቦርድ አባላቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባልሆኑ ባለአክሲዮኖች ተጠቁመው በእነዚሁ ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ፤ በሁሉም ባለአክሲዮኖች ተጠቁመው በሁሉም ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ፤ እንዲሁም በቦርዱ ተጠቁመው በሁሉም ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ ነጻና ገለልተኛ የሆኑ ዕጩ ዳይሬክተሮች ይሆናሉ፣
- የነፃና ገለልተኛ እጩዎች ጥቆማን ሳይጨምር የሁሉም ዳይሬክተሮች ጥቆማ እና ምርጫ የሚካሄደው በጉባዔው ዕለት ነው፣
- የባንኩ ባለአክሲዮን እራሱን ወይም ሌሎች ባለአክሲዮኖችንና ሠራተኞችን ለቦርድ አባል ዕጩነት መጠቆም ይችላል፣
- የጊዜያዊ የቦርድ አባላት ጥቆማ እና አስመራጭ ኮሚቴ አባል ለቦርድ አባልነት መጠቆም አይችልም፤
- ጥቆማ ሲሰጥ ቦርዱ በቂ የፆታ፤ የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ ስብጥር ሊኖረው የሚገባ መሆኑ ከግንዛቤ መወሰድ አለበት፤
- ባለአክሲዮኖች የሚጠቁሙትን ግለሰብ ወይም የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅትን ወክሎ የሚጠቆም የተፈጥሮ ሰውን የትምህርት ደረጃ፣ የስራ ልምድ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ በቂና ትክክለኛ መረጃን መስጠት አለባቸው፡፡
ማሳሰቢያ፡–
- ከላይ በወንድ ጾታ የተገለፀው ለሴት ፆታም ያገለግላል፣
- ከአጠቃላይ የቦርድ አባላት ውስጥ ቢያንስ ሁለቱ (2) ሴቶች መሆን አለባቸው፡፡